Quantcast
Channel: ተሟገት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1275

የገቢ ግብርና የታክስ አስተዳደር አዋጆችን ለማሻሻል ረቂቅ ሕጎች ለምክር ቤቱ ቀረቡ

$
0
0

የገቢ ግብርና የታክስ አስተዳደር አዋጆችን ለማሻሻል የቀረቡ ረቂቅ አዋጆችን ሰኔ 23 ቀን 2008 ዓ.ም. የተመለከተው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለቋሚ ኮሚቴዎች መራቸው፡፡

ምክር ቤቱ በዕለቱ ቀድሞ የተመለከተው የገቢ ግብር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ የተዘጋጀው የግብር ሥርዓቱ ከነባራዊ ሁኔታዎች ጋር በተጣጣመና የተሟላ ሆኖ የአገሪቱን የፊስካል ችግሮች በመፍታት ዘመናዊ ሥርዓት እንዲዘረጋና በየጊዜው የሚለዋወጠውን የኢኮኖሚ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ ነባሩን ሕግ ለማሻሻል በማስፈለጉ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም በሥራ ላይ ያለው አዋጅ ያለበትን ጉድለትን በማስተካከል ወቅታዊነቱን የጠበቀ እንዲሆን ታሳቢ መደረጉም ከረቂቅ አዋጁ ጋር ተያይዞ የቀረበው አባሪ ያመለክታል፡፡

ረቂቅ አዋጁ በርከት ያሉ ማሻሻያዎች የቀረቡበት ሲሆን፣ ግብር ተፈጻሚ በሚሆንባቸው ተቋማትና ድርጅቶች የግብር ምጣኔ እንዲሁም ከግብር ነፃ ስለሚሆኑባቸው ሥርዓትን ጨምሮ የማሻሻያ ድንጋጌዎችን አካቷል፡፡

ለአብነትም ያህል በንዑስ ተቋራጮች ላይ ቀድሞ ተጥሎ የነበረው የአሥር በመቶ ከተከፋይ ሒሳብ ላይ ተቀንሶ የሚቀር ግብር በነዳጅ ፍለጋ ላይ የተሰማሩትን እንዳይመለከት የማሻሻያ ሐሳብ ቀርቧል፡፡ ከግብር ነፃ የሚሆንበትን ድንጋጌም መካተት ከሚጠቀሱት የማሻሻያ ሐሳቦች አንዱ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት በማዕድን ማውጣት፣ በማኑፋክቸሪንግና በግብርና ሥራ የተሰማራ ቀጣሪ ለቀጣሪው የሚያቀርበው የምግብና መጠጥ ተቀናሽ የሚደረገው የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር በሚያወጣው መመርያ በሚቀመጠው ገደብ መሠረት መሆኑ ተመልክቷል፡፡ እንዲሁም ለመኖሪያ ቤት ሠራተኞች የሚከፈል ደመወዝ ከግብር ነፃ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

በተጨማሪም ከተከፋይ ሒሳብ ግብር ቀንሶ የመያዝ ግዴታ ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞችን የማይመለከት መሆኑንም ተገልጿል፡፡

በተያያዘ ዜናም በዕለቱ ቀርቦ በምክር ቤት አባላት ውይይት የተደረገበት የታክስ አስተዳደር አዋጁን ለማሻሻል የቀረበው ረቂቅ አዋጅ በበኩሉ ዘርዘር ያሉ ድንጋጌዎችን ለማሻሻል ሐሳብ አቅርቧል፡፡

ከእነዚህም ውስጥ ሀብት ስለመያዝ የሚደነግገውን አንቀጽ ማሻሻል አንዱ ነው፡፡ ረቂቅ አዋጁ የግብር ከፋዩን ሀብት ለመያዝ የሚቻለው ከሚፈለግበት ግብር ጋር ተመጣጣኝ በሆነ መጠን መሆኑን የሚመለከት የማሻሻያ ንዑስ አንቀጽ አካቷል፡፡

ግብርን ዘግይቶ በመክፈል የሚጣል መቀጫና ወለድ የሚደነግገው ድንጋጌ በግብር ከፋዩ ላይ የሚጣለውን በባንኮች ከፍተኛው የማበደሪያ ወለድ መጠን ላይ ታክሎ የሚከፈለውን 25 በመቶ መቀጫ ወደ 15 በመቶ ዝቅ እንዲል ተደርጓል፡፡

ለታክስ ይግባኝ ኮሚሽን ይግባኝ ስለማቅረብ የሚደነግገው አንቀጽ ተሰርዞ በአዲስ እንዲተካ ረቂቅ አዋጁ ያቀርባል፡፡ በነባሩ አዋጅ ግብር ከፋዩ ባቀረበው የቅሬታ አጣሪ የሥራ ክፍል በ180 ቀናት ውስጥ ውሳኔ ካልሰጠ ግብር ከፋዩ የተወሰነበትን ግብር 25 በመቶ አስይዞ ይግባኙን ለግብር ይግባኝ ኮሚሽን ሊያቀርብ እንደሚችል ያመለክታል፡፡ ነገር ግን የማሻሻያው አንቀጽ ይህንን የሚተካ ድንጋጌ አቅርቧል፡፡ በዚህም መሠረት ግብር ከፋዩ ይግባኝ ሊያቀርብ የሚችለው መቀጫና ወለድን ሳይጨምር የተወሰነበትን ግብር 50 በመቶ በማስያዝ ሊሆን እንደሚገባ ይገልጻል፡፡

ሁለቱንም ረቂቅ አዋጆች ያየው ምክር ቤቱ አስተያየቶችን ከሰጠባቸው በኋላ ለበጀትና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ እንዲሁም በተባባሪነት ለሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር ዕይታ መርቷቸዋል፡፡

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 1275

Trending Articles