የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ200 በላይ ድርጅቶችን መዝጋቱን አስታወቀ፡፡ ከእነዚህም መካከል 165 ድርጅቶች የተዘጉት በሕግ አግባብ ባለመመሥረታቸው ሲሆን፣ የቀሩት ደግሞ ፈንድ በማጣት፣ በራሳቸው ፈቃድና ጥያቄ ነው፡፡
ኤጀንሲው ከመዘገባቸው በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ጋር ከሰኔ 20 እስከ 21 ቀን 2008 ዓ.ም. በአዳማ በመከረበት ወቅት እንደተገለጸው፣ በሕግ አግባብ ሳይሠሩ ተደርሶባቸው የተዘጉ ድርጅቶች ንብረቶች በመጣራት ላይ ነው፡፡ በራሳቸው ጥያቄ የተዘጉ ድርጅቶች ንብረቶች ግን ተጣርተው በሥራ ላይ ላሉና የቁሳቁስ እጥረት ላሉባቸው ድርጅቶች በነፃ ተከፋፍለዋል፡፡ በሥራ ላይ ያሉና ንብረት ይወገድልኝ ጥያቄ ያቀረቡ 60 ድርጅቶች ደግሞ በጥያቄያቸው መሠረት ለመፈጸም እንቅስቃሴ መጀመሩ ተገልጿል፡፡
ኤጀንሲው በመላ አገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ከሁለት ሺሕ በላይ የሚሆኑ ድርጅቶች የሚገኙበትን ደረጃ መለየቱንም ገልጿል፡፡ ከዚህ አኳያ 169 ያህሉ የ‹‹ኤ›› ደረጃ፣ 673 ያህሉ የ‹‹ቢ›› ደረጃ እንዲሁም 1327 ያህሉ የ‹‹ሲ›› ደረጃ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ድርጅቶቹ ደረጃቸው ሊለያይ የቻለው ለዚህ ሲባል በወጣው መስፈርት መሠረት መሆኑም በውይይቱ ወቅት ተገልጿል፡፡
በምክክር መድረኩ እንደተወሳው፣ ድርጅቶቹ ለልማት የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ያህል ዘርፉ ብዙ ችግሮች አሉበት፡፡ ኤጀንሲው ባለፉት ዘጠኝ ወራት ባካሄደው ግምገማም፣ ከ700 በላይ የሚሆኑ ድርጅቶች ችግር ውስጥ መግባታቸውን ተገንዝቧል፡፡ ከተቋቋሙበት ዓላማ ውጭ መንቀሳቀስና ያለ ኤጀንሲው ፈቃድ ባንክ ሒሳብ መክፈት፣ የገቢ ምንጫቸውን አለማሳወቅና ዓመታዊ ሪፖርት በወቅቱ አለማቅረብ ከገቡባቸው ችግሮች ይጠቀሳሉ፡፡
አስተዳደራዊ ወጪን ከ30 በመቶ በላይ መጠቀምና ከዓላማ ማስፈጸሚያ ጋር መቀላቀል፣ ፕሮጀክት ስምምነት ሳይፈራረሙ መሥራት፣ ከኤጀንሲው ዕውቅና ውጪ የገቢ ማስገኛ ሥራ ላይ መሰማራት፣ ፕሮግራሞቻቸውን ከሃይማኖት ጋር አቀላቅለው መተግበር፣ ያልተፈቀደ አርማ መጠቀምም ከችግሮቹ መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡
እነዚህንም ችግሮች ለመፍታት ለድርጅቶቹ የመጀመሪያና የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያዎች መስጠታቸውም ተመልክቷል፡፡ በተጨማሪም ያሉባቸውን ክፍተቶች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ እንዲያስተካክሉ መደረጉና በዚህም አብዛኞቹ ክፍተታቸውን እያስተካከሉ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡
የኤጀንሲው ምክትል ዳይሬክተር ወይዘሮ ፋንታዬ ገዛኸኝ፣ ‹‹የልማት ፕሮግራማቸሁን ከሃይማኖት ጋር አስተሳስራችሁ የምትሠሩ ሚናችሁን ለዩ!›› ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የሃይማኖት ሥራ ለመሥራት የሚፈልጉ በአርብቶ አደርና ፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር፣ የበጎ አድራጎት ሥራ ለማከናወን ደግሞ በኤጀንሲው መመዝገብና ፈቃድ ማግኘት እንደሚገባቸው ጠቁመው፣ በተረፈ በበጎ አድራጎት ሥራ ላይ ሃይማኖትን አካትቶ መሥራት ሕገወጥ ተግባር መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የተዘጉ ድርጅቶችን ንብረቶች የመረከብ፣ ሥራ ላይ ያሉ ድርጅቶች ደግሞ የሚያቀርቡትን ንብረት ይወገድልኝ ጥያቄ የመቀበልና የማስፈጸም ኃላፊነት የወደቀው በኤጀንሲው ላይ ነው፡፡ በኃላፊነቱም መሠረት ከሚረከባቸው ንብረቶች መካከል ደህና የሆኑትን ለሌሎች ድርጅቶች ያከፋፍላል፣ ችግር ያለባቸውን ንብረቶች ደግሞ በሐራጅ ሸጦ በባንክ ዝግ ሒሳብ እንዲቀመጥ ያደርጋል፡፡ በዚህ መልኩ የተቀመጠው ገንዘብ በምን መልኩ ሥራ ላይ መዋል እንዳለበት ወደፊት እንደሚታይ ምክትል ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ አንፃር የቀድሞው አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽን ሀብት የነበሩ ልዩ ልዩ ንብረቶችን ለማስመለስ ኤጀንሲው ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ላይ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
የኤጀንሲው የንብረት ማጣራት፣ ማስተላለፍና ማስወገድ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዳኜ ሽብሩ እንደሚሉት፣ ንብረትን የማጣራት፣ የማስተላለፍና የማስወገድ ሥራ እንደታሰበው አልተንቀሳቀሰም፡፡ ኤጀንሲው ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ያልተወገዱ የድርጅቶች ንብረቶች መብዛትና ይህንን ተግባር ለማከናወን የተመደበው የሰው ኃይል ቁጥጥር ማነስም ችግሩን እንዳጎላው ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያን ከድህነት ለማውጣትና መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሰለፍ በሚካሄደው እንቅስቃሴ ላይ የኢትዮጵያ ነዋሪዎች በጎ አድራጎት ድርጀቶችና ኅብረቶች ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸውና አስተዋጽኦዋቸውንም የሚያበረክቱት በየተሰማሩበት አካባቢ የደሃ ደሃ የሆነውን ማኅበረሰብ ትኩረት ባደረገ መልኩ ሲሠሩ መሆኑም በውይይቱ ተነስቷል፡፡
