- በሶዶ አካባቢ የ3G ኔትወርክ መዘርጋት ጀምሯል
በዓለም የቴሌኮም ቴክኖሎጂና መሠረተ ልማት አቅርቦት ላይ ቁንጮ በመሆን የስዊድኑን ኤሪክሰንን ደረጃ የተረከበው ሁዋዌ ቴክኖሎጂስ ኮርፖሬሽን፣ ከዚህ ቀደም ለኤሪክሰን ተመድበው ከነበሩ የኔትወርክ ዝርጋታ መስመሮች የተወሰኑትን መረከብ መጀመሩ ተሰማ፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም ከሁለት ዓመት በፊት ለሌላኛው የቻይና ቴሌኮም ኩባንያ ዜድቲኢ ተሰጥቶ የነበረውን ድርሻ በመንጠቅ ለኤሪክሰን መስጠቱ አይዘነጋም፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት የተጀመረው የ1.6 ቢሊዮን ዶላር የቴሌኮም ኔትወርክ ማስፋፈፊያ ፕሮጀክትን ለሁለት ተጋርተው ወደ ሥራ የገቡት ሁዋዌና ዜድቲኢ ነበሩ፡፡ ሁለቱም እኩል የ800 ሚሊዮን ዶላር ድርሻ እንዲይዙ ቢደረግም፣ ዜድቲኢ አሳይቷል በተባለው መጓተት ሳቢያ ኤሪክሰን የተወሰኑ የኔትወርክ መስመሮችን ከዜድቲኢ እንዲረከብ ተደርጎ ነበር፡፡
ይህ ከሆነም በኋላ ሁዋዌ ጥቂት የማይባሉ የቴሌኮም መስመሮችን ሲረከብ የቆየ ሲሆን፣ በቅርቡ ግን ኤሪክሰን ሊገነባ ካልቻላቸው መስመሮች መካከል አንዱን ተረክቦ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ የሪፖርተር ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡ ከአዲስ አበባ የ4G ኔትወርክ ዝርጋታ ባሻገር፣ በሰሜን፣ በሰሜን ምሥራቅ፣ በሰሜን ደቡብ፣ በምሥራቅ እንዲሁም በአፋር አካባቢ ያሉ ስድስት የኔትወርክ ዝርጋታ መሥመሮችን ተረክቦ በመሥራት ላይ የሚገኘው ሁዋዌ፣ አሁን ደግሞ ደቡብ ደቡብ ምዕራብ ሪጅን ተብሎ ከሚጠራው መስመር ውስጥ የሶዶ አካባቢን ተረከቦ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ከሁዋዌ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡ በመሆኑም የሶዶ አካባቢ የ3G ኔትወርክ አገልግሎት ለማግኘት መቃረቡ ታውቋል፡፡
እንዲህ ባለው ሁኔታ በአገር ውስጥ ያለው ይዞታ እየጎላ የመጣው ሁዋዌ በዓለም አቀፍ ደረጃም ተቀናቃኞቹን መጋፈጥ ጀምሯል፡፡ በቅርቡ ዎል ስትሪት ጆርናል ባወጣው ዘገባ መሠረት፣ ሁዋዌ በፓተንት መብት ጥሰት ሳቢያ ሳምሰንግን ከሷል፡፡ የክሱ መነሻም ሳምሰን የሁዋዌ ውጤቶች የሆኑ 11 የባለቤትነት መብት የተከበረላቸውን ምርቶች ያለፈቃድ ተጠቅሟል የሚል ነው፡፡ ሁዋዌ ባቀረበው ክስ መሠረት፣ በ4G አማካይነት የስማርት ስልኮችና የሴሉላር ኔትወርክ ያለምንም መቆራረጥ ለመጠቀም የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን ሳምሰንግ ያለፈቃድ ሲጠቀም ተገኝቷል፡፡
ከዚህ ባሻገር ሳምሰንግና አፕል ኩባንያዎችን በስማርት ስልኮች አምራችነት ቀድሞ ለመሰለፍ ማቀዱ በዎል ስትሪት ጆርናል የተዘገበለት ሁዋዌ፣ ለጥናትና ለምርምር ከፍተኛ ወጪ በመመደብም እነ አፕልን በልጦ መቀመጡ ተዘግቦለታል፡፡
በአገር ውስጥ ኢትዮ ቴሌኮም የፕሮጀክት መጠኑን ስፋቱን እንዲሁም ሊያከወናውን ባሰበው አዲስ የኔትወርክ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት ያሳየው ሁዋዌ፣ ከወዲሁ የፍላጎት መግለጫ ሰነዶቹን ለኢትዮ ቴሌኮም ማስገባቱም ታውቋል፡፡
