በሕገወጥ ንግድ ግብር ማጭበርበር ወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብና ከአገር በማሸሽ 871,410,695 ብር በመንግሥት ላይ ጉዳት በማድረስ የተጠረጠሩ አንድ ኢትዮጵያዊ፣ 16 የውጭ አገር ዜጎችና ድርጅቶች የተመሠረተባቸውን ክስ እንዲከላከሉ ሰኔ 23 ቀን 2008 ዓ.ም. ብይን ተሰጠ፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ከሁለት ዓመት በፊት የመሠረተውን የወንጀል ክስ ሲመረምር የከረመው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ሰኔ 23 ቀን 2008 ዓ.ም. በሰጠው ብይን እንደገለጸው፣ በክስ መዝገቡ ሁለተኛ ተከሳሽ የነበሩት የጂቡቲ ዜግነት ያላቸው ሲና መሐመድ መሐሙድ ከተመሠረተባቸው ክስ በነፃ ተሰናብተዋል፡፡ የኒውዚላንድ ዜግነት ያላቸው ሱሀስ ፓራሳድና የህንድ ዜግነት ያላቸው አሾክ ሞሃንላል ሻርማ ክስ የተመሠረተባቸው በሌሉበት በመሆኑ ክሳቸው ተቋርጧል፡፡ በፌዴራል ማረሚያ ቤት ሆነው ሲከራከሩ በከረሙት ኢትዮጵያዊው አሽረፍ አወልና ኦካፔ ኢምፔክስ፣ ሲሪላንካዊዎቹ ሂትራጅግ ያሳንታ፣ ፕላንዋታጅ አሲታ፣ ቦፒ ጊድራ አጅት ኩማር፣ ኩሩፑ አራችችግ፣ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ዜግነት የተመዘገቡና በጠበቃ የተወከሉት ዱባይ ኦቶ ጋለሪ ኤልኤልሲና ኦቶ ወርልድ ኢንተርናሽናል ፍሪዞን ኩባንያዎች ላይ ዓቃቤ ሕግ ባቀረባቸው የሰነድ ማስረጃዎችና ምስክሮች እንደ ክሱ ማስመስከሩን ገልጾ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል፡፡
በሌሉበት ክስ የተመሠረተባቸው ስሪላንካዊው አሳንታ ኡዳያ ኩማራ፣ ህንዳዊዎቹ አንኪት ሙኪሽ መሂታ፣ ኩማር ኤም ላክሃኒና ቪሻል ኩማር ላክሃኒ፣ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የሚኖሩት ሙኒሽ ኩማር ላክሃናና መሐመድ ሽፋን መሐመድም የተመሠረተባቸውን ክስ እንዲከላሉ ፍርድ ቤቱ ብይን ሰጥቷል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ የወንጀል ድርጊቱን የፈጸሙት ዱባይ ኦቶ ጋለሪ ኤልኤልሲና አውቶ ወርልድ ኢንተርናሽናል ፍሪ ዞን ኩባንያ፣ በ2000 ዓ.ም. ባለሁለትና ሦስት እግር ተሽከርካሪዎች (ባጃጅ) ማምረቻና መገጣጠሚያ ፋብሪካ በኢትዮጵያ ለመክፈት የኢንቨስትመንት ፍቃድ ከወሰዱ በኋላ ፋብሪካውን መክፈት በመተው በማስመጣት ሥራ ላይ በመሰማራት መሆኑን ዓቃቤ ሕግ በሰነድና በምስክሮቹ ማስረዳቱን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡
ከድርጅቱ ባለቤቶች መካከል ቪሻል ኩማር ላክሃኒ የተባሉት ተከሳሽ ኤዢያ አፍሮ አውቶ ሞቢልስ የሚል የግል ድርጅት በማቋቋምና ባጃጅ የማምረቻና መገጣጠሚያ ፋብሪካ ለመክፈት የወሰዱትን ፍቃድ ወደ ጎን በመተው፣ የፀና የንግድ ፍቃድ ሳይኖራቸው በውጭ አገር የተመረቱ ባለሁለትና ሦስት እግር ተሽከርካሪዎችን ወደ ኢትዮጵያ በማስገባት፣ በጅምላና በችርቻሮ ሲሸጡ በሕገወጥ ንግድና በግብር ሥወራ ያገኙን 350,881,546 ብር ከአገር ማሸሻቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱና በምስክሮቹ አብራርቷል፡፡ በመሆኑም ተከሳሹ የፀና የንግድ ፍቃድ ሳይኖራቸውና ለኢትዮጵያውያውን የተከለለ ሥራን በመሥራታቸው፣ የገቢ ግብርና የተጨማሪ እሴት ታክስ አሳውቀው ባለመክፈላቸውና በወንጀል ተግባር የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስለው መሥራታቸውን ዓቃቤ ሕግ በሰውና በሰነድ ማስረዳቱን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡
ቪሻል ኩማር ላክሃኒ በሕገወጥ መንገድ ያገኙትን ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ከአገር ካወጡ በኋላ ተመልሰው ወደ ኢትዮጵያ በመምጣትና በኢትዮጵያዊው ዜጋ አቶ አሽረፍ አወል አብዶና በነፃ በተሰናበቱት የጂቡቲ ዜጋ ሲና መሐመድ ባለቤትነት በኢትዮጵያ የተመዘገበውን አካፔ ኢምፔክስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በሽፋንነት መጠቀማቸውን የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች መመስከራቸውን ፍርድ ቤቱ በብይኑ ገልጿል፡፡ ማኅበሩን በሽፋንነት በመጠቀም ዱባይ ኦቶ ጋለሪ ኤልኤልሲና ኦቶ ወርልድ ኢንተርናሽናል ፍሪ ዞን ኩባንያ በዱባይ የሚያመርቷቸውን ባጃጆች ወደ ኢትዮጵያ በማስላክ ለኢትዮጵያውያኖች ብቻ የተፈቀደውን የአስመጭነት፣ የጅምላና ችርቻሮ አከፋፋይነት ንግድ ሥራ ላይ ተሰማርተው ሕገወጥ ንግድ በመሥራት 520,529,149 ብር ወደ ውጭ ማሸሻቸውን ዓቃቤ ሕግ ማስመስከሩን ፍርድ ቤቱ በብይን ተናግሯል፡፡ በቂ የሰነድ ማስረጃዎችን ማቅረቡንም አክሏል፡፡
ኩማር ኤምላክሃኒ፣ ቪሻል ኩማረ ላክሃኒ፣ ሙኒሽ ኩማር ላክሃኒና መሐመድ ሽፋን መሐመድ የተባሉት ተከሳሾች ከላይ የተጠቀሱትን የሲሪላንካ ዜግነት ያላቸውን ሰዎች በዱባይ በሚገኘው ድርጅታቸው በመቅጠር (ባጃጅ የሚላክበት ድርጅት) ባጃጆቹን ወደ ኢትዮጵያ እንዲልኩ ሲያደርጉ፣ ኢትዮጵያዊው አሽረፍ አወል ደግሞ ሥራ አስኪያጅ ሆነው የሚሠሩበት ኦካፔ ኤምፔክስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሠራተኞች እንደሆኑ በማስመሰል ሐሰተኛ የቅጥር ውል በመፈረም በኢትዮጵያ የመኖሪያ ፈቃድ እንዲያገኙ ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በሰነድና በምስክር ማስረዳቱን ፍርድ ቤቱ በብይኑ ተናግሯል፡፡
በመሆኑም ተከሳሾቹ ከ2004 ዓ.ም. እስከ 2006 ዓ.ም. ድረስ ምንም ዓይነት የፀና ፍቃድ ሳይኖራቸው ባለሁለትና ሦስት እግር ባጃጅ በማስመጣት በጅምላና ችርቻሮ የንግድ ሥራ ላይ ተሰማርተው መክረማቸውን በምስክሮቹ ዓቃቤ ሕግ ሊያስረዳ መቻሉን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ ተከሳሾቹ በአጠቃላይ የባጃጅ ማምረቻና መገጣጠሚያ ለመክፈት በሚልና አካፔ ኢምፔክስን ሽፋን በማድረግ በሕገወጥ መንገድ መንግሥትን 871,410,695 ብር ማሳጣታቸውን ዓቃቤ ሕግ በሰውና በሰነድ ማስረጃዎች እንደ ክሱ ማስረዳት መቻሉን ፍርድ ቤቱ ገልጾ፣ ተከሳሾቹ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል፡፡ ተከሳሾቹ ገንዘቡን ሊያሸሹ የቻሉት ጂቡቲ በሚገኘው ኤስዲሲ በርበራ ፍሪ ዞን ኩባንያ፣ ቢሲአይኤምአር ባንክና ዳሞኮ ሎጂስቲክስ ኩባንያ (ኬንያ፣ ጂቡቲና ዱባይ የሚገኙ) በኩል መሆኑ ዓቃቤ ሕግ ባቀረባቸው ሰነዶች ማስመስከሩንም ፍርድ ቤቱ አክሏል፡፡
የውጭ አገር ተከሳሾቹ የአገሪቱን የኢሚግሬሽን አዋጅና ደንቦችን በመጣስ በቱሪስት ቪዛ ገብተው በሕገወጥ መንገድ ሲሠሩ መገኘታቸውንም በማስረጃዎች ማስመስከር በመቻሉ ተሸሳሾች ከጥቅምት 7 እስከ 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ መከላከያ ምስክሮቻቸውን እንዲያሰሙ ብይን ሰጥቷል፡፡
