Quantcast
Channel: ተሟገት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1275

የቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲ ልሳን ዋና አዘጋጅ ዋስትና ተከለከለ

$
0
0

‹ነገረ ኢትዮጵያ› በሚል ስያሜ ይታተም የነበረው የሰማያዊ ፓርቲ ልሳን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አቶ ጌታቸው ሽፈራው የዋስትና ጥያቄው ውድቅ ተደረገ፡፡

ተከሶበት የነበረው የሽብር ተግባር ወንጀል ክስ ተቀይሮ ወደ መደበኛ ክስ በመቀየሩና የተጠቀሰበት የወንጀል ሕግ አንቀጽ 257 (ሀ እና መ) ዋስትና ባለመከልከሉ፣   አቶ ጌታቸው ያቀረበውን የዋስትና ጥያቄ መርምሮ ለታኅሳስ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት ነበር፡፡

ፍርድ ቤቱ በዕለቱ እንደገለጸው የአቶ ጌታቸውን ሕገ መንግሥታዊ የዋስትና መብት ጥያቄን ሲመረምር፣ ተከሳሹ ሕጋዊና መደበኛ የሚታወቅ የመኖሪያ አድራሻ እንዳለው ማረጋገጡን ከክርክሩ መረዳቱን ነው፡፡ ነገር ግን ዓቃቤ ሕግ ባቀረበው መቃወሚያ ተመሥርቶበት የነበረው የሽብር ድርጊት ወንጀል ተፈጽሟል የተባለው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ሆኖ ከተፈረጀው የግንቦት ሰባት ጋር በመሆኑ፣  በዋስትና ቢለቀቅ በተለያየ መንገድ ከአገር ሊወጣና ሊቀርብ እንደማይችል ማስረዳቱን ፍርድ ቤቱ አስታውቋል፡፡

በመሆኑም ለተከሳሹ የተቀየረው የሕግ አንቀጽ በመርህ ደረጃ ዋስትና የማይከለክል ቢሆንም፣ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 67 (ሀ) መሠረት መመልከቱ አስፈላጊ መሆኑን እንዳመነበትም ገልጿል፡፡

በመሆኑም ዓቃቤ ሕግ እንዳቀረበው መቃወሚያና ተከሳሹ እንደሚያቀርብ የገለጻቸው መከላከያ ምስክሮች እንደክሱ ባያስረዱለት ሊያስቀጣው የሚችለውን ከፍተኛ የአሥር ዓመት እስራት ቅጣት በመፍራት፣ በተለያየ አኳኋን ወይም አቅጣጫ ከአገር ሊወጣ ይችላል የሚል ግንዛቤ ፍርድ ቤቱ መውሰዱን አስረድቷል፡፡ በመሆኑም በወ/መ/ሥ/ሥ/ቁጥር 67 (ሀ) መሠረት የዋስትና ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ የመከላከያ ምስክሮቹን ለየካቲት 7 ቀን 2009 ዓ.ም. እንዲያቀርብ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 1275

Trending Articles