በገዥው ፓርቲ የግምገማ መድረኮች የማይጋለጡ ውስብስብ የሙስና ወንጀሎችን በልዩ ጥናት ፈትሾ እንደሚያወጣ፣ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ገለጸ፡፡
ኮሚቴው ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ ለሕዝብ በገባው ቃል መሠረት፣ ‹‹በጥልቀት የመታደስ›› ዘመቻው በጥሩ ሁኔታ በመተግበር ላይ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
በዚህ ሒደት ፀረ ዴሞክራሲ፣ አድርባይነት፣ በትስስር የመሥራት አሠራሮችን በማረም በአባላቱና በአመራሮች መካከል ‹‹ጓዳዊ ትስስርን›› በማጣመር፣ መተማመንን በሚያጎለብት ሁኔታ መፈጸሙን ገልጿል፡፡
በድርጅቱ ውስጥ በተደረጉ ትግሎች ሙስናና ብልሹ አሠራሮች በየትኛውም ደረጃና መልኩ የሚገለጹ ቢሆንም፣ ያለምንም ምሕረት ፖለቲካዊ ትግል በማድረግ መጋለጣቸውን ያስረዳል፡፡ ከዚህ በመነሳትም ፖለቲካዊ፣ አስተዳደራዊና ሕጋዊ ዕርምጃዎች መወሰዳቸውን ይገልጻል፡፡
በግምገማ መድረክ የማይጋለጡ ከሙስና ውስብስብ ባህሪያት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በሚመለከት፣ በሁሉም ደረጃዎች ጥናቶችና ፍተሻዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ መወሰኑን አብራርቷል፡፡
በጋምቤላ የሰፋፊ እርሻዎች ኢንቨስትመንትን አስመልክቶ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተዋቀረ ኮሚቴ ያጠናው ጥናት በቅርቡ ይፋ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
በዚህም ጥናት ከባንክ ብድር ጋር በተያያዙ ብልሹ አሠራሮችና ትስስር የቀረጥ ነፃ መብት መበዝበዝ እንደነበር ተገልጿል፡፡
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ የፌዴራል ፖሊስ በሰጠው መግለጫ፣ በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ 130 ግለሰቦችና ባለሥልጣናት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ይፋ አድርጓል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ የተያዙት ከመንግሥት ዕቃ ግዥ፣ ከቤቶች ልማት፣ ከመሬት ልማት፣ ከባንክ ሥራዎችና ከአክሲዮን ኩባንያዎች፣ ከታክስ ማጭበርበር ጋር መሆኑን ገልጿል፡፡
