Quantcast
Channel: ተሟገት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1275

ጃፓን ከ40 ዓመታት በኋላ የ50 ሚሊዮን ዶላር የረጅም ጊዜ ብድር ለኢትዮጵያ አቀረበች

$
0
0

 

ላለፉት 43 ዓመታት ያህል ተቋርጦ የቆየውን የብድር አቅርቦት በማስቀጠል፣ ጃፓን የመጀመሪያውን የ50 ሚሊዮን ዶላር የረዥም ጊዜ ብድር ለኢትዮጵያ አቀረበች፡፡

በኢትዮጵያና በጃፓን መንግሥታት መካከል በተደረገ ስምምነት መሠረት፣ ብድሩ ለሴቶች የፈጠራ ሥራዎች እንደሚውል ተገልጿል፡፡ ዓርብ የካቲት 17 ቀን 2009 ዓ.ም. በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስቴር የተካሄደውን የብድር ስምምነት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አድማሱ ነበበ፣ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺኒቺ ሳይዳ እንዲሁም፣ የጃፓን ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ የኢትዮጵያ ወኪል ኪሚያኪ ጂን ተፈራርመዋል፡፡

በስምምነቱ መሠረት ለመጪዎቹ ሁለት ዓመታት የሚቆይ የፈጠራ ሥራ ሐሳብ ያላቸው ሴቶች ይደገፉበታል የተባለውን የ50 ሚሊዮን ዶላር የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡ ባንኩ ሴቶችን ለሚደግፉ አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች ገንዘቡን በመልቀቅ ለተጠቃሚዎች እንዲያቀርቡ የማድረግ ኃላፊነት እንደሚኖረው ታውቋል፡፡

ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ማክተም ጋር አብሮ የተቋረጠው የጃፓን የብድር አቅርቦት፣ ከ43 ዓመታት በፊት ለከርሰ ምድር ውኃ ልማት ፕሮጀክት፣ እንዲሁም ለአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ተርሚናል ግንባታ ማስፈጸሚያ የዋለ ብድር መልቀቁን አምባሳደር ሳይዳ አስታውሰዋል፡፡

ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚገልጸው፣ የ50 ሚሊዮን ዶላር ብድሩ በ40 ዓመታት ጊዜ ውስጥ የሚከፈል ሲሆን፣ የአሥር ዓመት የዕፎይታ ጊዜ ይኖረዋል፡፡ ከዕፎይታ ጊዜው በኋላ በየዓመቱ የ0.01 በመቶ ወለድ እየታሰበበት ከዋናው ብድር ጋር አብሮ እንደሚከፈል ለማወቅ ተችሏል፡፡

ላለፉት በርካታ ዓመታት የጃፓን መንግሥት በኦፊሴል የልማት ትብብር መስክ የዲፕሎማሲ ግንኙነትና ትብብር ከሚያደርግባቸው አገሮች ጋር የ20 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ መስጠቱን መረጃዎቸ ይጠቁማሉ፡፡ ከሰሃራ በታች ለሚገኙ አገሮችም የ1.5 ቢሊዮን ዶላር የብድርና የዕርዳታ ድጋፍ እንደተረደገ ከጃፓን ኤምባሲ ለማወቅ ተችሏል፡፡

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 1275

Trending Articles