Quantcast
Channel: ተሟገት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1275

የደቡብ ሱዳን ነፃ አውጪ ግንባር የቀድሞ ኤታ ማጆር ሹም ኢትዮጵያ በፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ላይ ግፊት እንድታደርግ አሳሰቡ

$
0
0

 

-ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን ዘጠኝ የትብብር ስምምነቶች ተፈራረሙ

የቀድሞ የደቡብ ሱዳን ነፃ አውጪ ግንባር ኤታ ማጆር ሹም ጄኔራል ኦያይ ደንግ አጃክ፣ ኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ለሰላም ስምምነቱ ተገዢ እንዲሆኑ ወይም ከሥልጠናቸው ይለቁ ዘንድ ጫና እንድታደርግ አሳሰቡ፡፡

ካለፈው ሐሙስ የካቲት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ቀናት በአዲስ አበባ የሥራ ጉብኝት በማድረግ ላይ የነበሩት የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝን ጨምሮ ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በሁለትዮሽና በቀጣናው ሰላምና ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

በነሐሴ ወር 2008 ዓ.ም. በሁለቱም የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ወገኖች መካከል የተፈረመው ስምምነት ተግባራዊ ሳይሆን ከዓመት በላይ ቆይቷል፡፡ የሰላም ሒደቱን የመራው የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥት ድርጅት (ኢጋድ) ሊቀመንበር የሆነችው ኢትዮጵያ፣ ለስምምነቱ አለመፈጸም ምክንያት የሆኑት በሥልጣን ላይ ያሉት ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ላይ ግፊት እንድታደርግ ጄኔራሉ አጥብቀው ጠይቀዋል፡፡

ጄኔራል ኦያይ የነፃ አውጪውን ጦር ግንባር በበላይነት የመሩ ሲሆኑ፣ አገሪቱ ነፃነቷን ከተቀዳጀች ጀምሮም በተለያዩ ከፍተኛ ኃላፊነቶች አገልግለዋል፡፡ በተለይ የብሔራዊ ደኅንነቱን፣ ቀጥለውም ብሔራዊ ኢንቨስትመንቱን በሚኒስትርነት የመሩት ጄኔራሉ፣ በፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተጠርጥረው  ለስድስት ወራት በእስር ካሳለፉ 13 ሚኒስትሮች መካከል ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት በደቡብ ሱዳን ከፍተኛ ጦርነት እንዳለና የአገሪቱ ሕዝብ ለስደት እየተዳረገና እየተሰቃየ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ውጊያ መኖሩንና ሰላም ፈጽሞ የጠፋ መሆኑን የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ እንዲገነዘብ የጠየቁት ጄኔራል ኦያይ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት እንደወዳጅ ጎረቤት በፕሬዚዳንቱ የሐሰት ንግግር ሳይሞኝ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

ጄኔራል ኦያይ በአሁኑ ወቅት ከዋና ተፋላሚው ከዶ/ር ሪክ ማቻር ጋር በመሆን ፕሬዚዳንቱን የሚቃወሙ ሲሆኑ፣ ይህንን የተናገሩት ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ነው፡፡ ጄኔራሉ እንደሚሉት፣ የስምምነቱ አካል የሆነው ብሔራዊ ውይይት በገለልተኛ አካል እንዲመራና ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር የድርድሩ አካል እንዲሆኑ፣ ወይም ከሥልጣናቸው እንዲወርዱና በአገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን ኢትዮጵያ የበኩሏን ሚና እንድትጫወት ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ከዚህ ውጪ ደቡብ ሱዳን መንግሥት አልባ የመሆን ዕድሏ ከፍተኛ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ሰሞኑን በኢትዮጵያ ይፋ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ ባለፈው ዓርብ የካቲት 17 ቀን 2009 ዓ.ም. ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን ዘጠኝ የትብብር ስምምነቶችን ተፈራርመዋል፡፡ በስምምነቶቹ መሠረት የሁለት መንገዶች ግንባታ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው ተብሏል፡፡ በኢነርጂ፣ በድንበር አካባቢ የንግድ ፕሮቶኮል፣ ለመደበኛ ንግድ፣ ለኮሙዩኒኬሽን፣ ለኢንፎርሜሽንና ለሚዲያ ደግሞ የመግባቢያ ሰነድ ተፈርሟል፡፡ ሁለቱም አገሮች በአሁኑ ወቅት ያላቸው መልካም ግንኙነት የበለጠ እንዲጠናከር ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ በፀጥታ፣ በንግድ፣ በልማትና በመሠረተ ልማት የበለጠ አብሮ ለመሥራት መስማማታቸውን አስታውቀዋል፡፡ 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 1275

Trending Articles