Quantcast
Channel: ተሟገት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1275

ከ152 ሚሊዮን ብር በላይ የውጭ ምንዛሪ አሳጥተዋል የተባሉ የቡና ነጋዴዎችና የመንግሥት ሠራተኞች ተከሰሱ

$
0
0

ሐሰተኛ ሰነድ ወይም ንግድ ፈቃድ በማቅረብና የብቃት ማረጋገጫ ባለሙያ ከሆኑ የመንግሥት ሠራተኞች ጋር በመመሳጠርና በጥቅም በመተሳሰር መንግሥት ከ152 ሚሊዮን ብር በላይ የውጭ ምንዛሪ እንዲያጣ አድርገዋል የተባሉ ቡና ነጋዴዎችና የመንግሥት ሠራተኞች፣ የካቲት 20 እና 21 ቀን 2009 ዓ.ም. ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

በተከሳሾቹ ላይ ሁለት የተለያዩ የክስ መዝገቦች ቀርበዋል፡፡ በግብርና ሚኒስቴር የብቃት ማረጋገጫ ባለሙያዎቹ አቶ ታምራት ኃይሌና አቶ ሁምኔሳ አብደታ፣ በግል ሥራ የሚተዳደሩትና ያልተያዙት አቶ ተመስገን ማሞ፣ ቡና ነጋዴዎቹ አቶ በርሄ ሐጐስና አቶ ዳንኤል ወልዴ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 18ኛ ወንጀል ችሎት ክስ ተመሥርቶባቸዋል፡፡ በሌላ መዝገብ ደግሞ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት የካቲት 21 ቀን 2009 ዓ.ም. ክስ የተመሠረተባቸውና በግል ሥራ እንደሚተዳደሩ የተገለጸው አቶ እስክንድር ፍቅሩ፣ አቶ ልዑል ሰገድ ግርማ፣ አቶ ኤሊያስ ጀማል፣ አቶ አብደላ ናስርና አቶ ዮናስ ታደሰ ደግሞ ሐሰተኛ ሰነዶችን በማዘጋጀትና ቡና ገዝተው በመሰወር ተከሰዋል፡፡

የመንግሥት ሠራተኞቹ የብቃት ማረጋገጫ ሲሰጡ ግብርና ሚኒስቴር በ2004 ዓ.ም. ባወጣው መመርያ ቁጥር 66114 መሠረት ነጋዴው ማሟላት የሚገባቸውን መሥፈርቶችን ማለትም መጋዘንና ቢሮ መከራየቱን፣ ለሥራው አስፈላጊ የሆኑ ባለሙያዎች መቀጠራቸውን በአካል ተገኝተው ማረጋገጥ ሲገባቸው ከአቶ በርሄና ከአቶ ዳንኤል ጋር ባላቸው ድብቅ የጥቅም ግንኙነት ምክንያት ሳያረጋግጡ፣ የብቃት ማረጋገጫ መስጠታቸውን የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው ክስ ያስረዳል፡፡

ባለሙያዎቹ በቀረበላቸው ፎርም ላይ በመሙላትና የቡና ላኪነት የብቃት ማረጋገጫ ከመስጠታቸውም በተጨማሪ፣ በተሰጣቸው ፈቃድ መሠረት መላክ አለመላካቸውን ሳያረጋግጡ የፈቃድ ዕድሳት መስጠታቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሷል፡፡ በመሆኑም ነጋዴዎቹ (አቶ በርሄና አቶ ዳንኤል) በተሰጣቸው የብቃት ማረጋገጫ መሠረት በአቶ ተመስገን ማሞ ስም ንግድ ፈቃድ በማውጣት ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ 274.3 ቶን (2,743 ኩንታል) ቡና መግዛታቸውንም አክሏል፡፡ ለመጋዘን ፍሳሽና እርጥበት ቅናሽ ተደርጎ የሚቀረውን 235.6 ቶን (2,356 ኩንታል) ቡና ወደ ውጭ በመላክ 894,179 ዶላር ወይም 14,655,604 ብር የውጭ ምንዛሪ መንግሥት እንዲያኝ ማድረግ ሲገባቸው፣ ቡናውን በመሰወር የውጭ ምንዛሪው እንዳይገኝ ማድረጋቸውንና ጉዳት ማድረሳቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡ ሁለቱ የቡና ነጋዴዎች በሌላ ጊዜ ደግሞ ሰለሞን አርዓያ (ያልተያዘ) የተባለውን ተከሳሽ ስም ተጠቅመው ንግድ ፈቃድ በማውጣት ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ የገዙትን 1,905.36 ቶን (19,053.6 ኩንታል) ቡና ወደ ውጭ ሳይልኩ በመሰወር መንግሥት ሊያገኝ የሚገባውን 6,502,895 ዶላር ወይም 129,407,612 ብር የውጭ ምንዛሪ ማሳጣታቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሮ አቅርቧል፡፡

አቶ እስክንድር፣ አቶ ልዑል ሰገድ፣ አቶ ኤልያስ፣ አቶ አብደላና አቶ ዮናስ የተባሉ ተከሳሾች ደግሞ ሐሰተኛ ሰነድ በማሠራት፣ ሐሰተኛ ሰነዱን በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽሕፈት ቤት አቅርበው ውክልና በመውሰድና ከግብርና ሚኒስቴር ለንግድ ሚኒስቴር የተጻፈና ማርቆስ ሰለሞን አበበ ለተባለ ቡና ላኪ ድርጅት የተሰጠ የሚመስል ሐሰተኛ የቡና ላኪነት የብቃት ማረጋገጫ በማዘጋጀት፣ ሚካኤል ወርቁ መንገሻ ለሚባል ግለሰብ ውክልና መስጠታቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያም ግምቱ 211,011 ዶላር ወይም 4,091,519 ብር የሆነ ቡና ገዝተው ወደ ውጭ መላክ ሲገባቸው ሳይልኩ በመሰወራቸው፣ የተጠቀሰውን ያህል ገንዘብ የውጭ ምንዛሪ ማሳጣታቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጾ አቅርቧል፡፡

እስክንድር ፍቅሩ በተባለው ተከሳሽ ውክልና በሚንቀሳቀሰው ዮታ ኮፊ ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ በተባለ ድርጅት ንግድ ፈቃድ በቡና ላኪነት ኤሊያስ ከተባለው ተከሳሽ ጋር ተስማምተው በጋራ ሲሠሩ፣ የቡና ጥራት ቁጥጥርና ግብይት አዋጅ ቁጥር 602/2000 አንቀጽ 8(3)ን እና አንቀጽ 14(5)ን በመተላለፍ ከምርት ገበያው የገዙትን 147.39 ቶን (1,473.9 ኩንታል) ቡና በመሰወር መንግሥት ማግኘት የሚገባውን 424,996 ዶላር ወይም 4,492,633 ብር የውጭ ምንዛሪ ማሳጣታቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡

በአጠቃላይ ተከሳሾቹ በድምሩ 152,647,368 ብር የውጭ ምንዛሪ በማሳጣታቸው የመንግሥትን ሥራ በማያመች አኳኋን መምራት ወንጀል፣ በከባድ አታላይነት ወንጀል፣ በአገር ኢኮኖሚ ላይ የሚፈጸም ወንጀል፣ ያላግባብ ፈቃድ መስጠትና ማፅደቅ ወንጀል፣ መንግሥታዊ ሰነዶችን አስመስሎ ማዘጋጀትና መገልገል ወንጀል ክስ መሥርቶባቸዋል፡፡

ችሎቶቹም ለቀረቡት ተከሳሾች ክሱ እንዲደርሳቸው ካደረጉ በኋላ በንባብ አሰምተው፣ የቅድመ ክስ መቃወሚያ ካላቸው ከጠበቆቻቸው ጋር ተመካክረው እንዲቀርቡ፣ ያልተያዙትን ፖሊስ ተከታትሎ በመያዝ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ በማስተላለፍ ለየካቲት 30 እና መጋቢት 7 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥተዋል፡፡

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 1275

Trending Articles