Quantcast
Channel: ተሟገት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1275

ለሞ ኢብራሒም ሽልማት የሚመጥን አፍሪካዊ መሪ አሁንም አልተገኘም

$
0
0

በአፍሪካ የአመራር ስኬት ሽልማት ለመስጠት በማቀድ እ.ኤ.አ. በ2016 በዚሁ ዘርፍ ከሥልጣን የለቀቁ የአፍሪካ መሪዎችን ቢያወዳድርም፣ የወጣውን ከፍ ያለ ደረጃ በማሟላት የሚያሸንፍ መሪ አለመገኘቱን ሞ ኢብራሒም ፋውንዴሽን ማክሰኞ የካቲት 21 ቀን 2009 ዓ.ም. አስታወቀ፡፡

በቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ዶ/ር ሳሊም አህመድ ሳሊም የሚመራው የሽልማት ኮሚቴና የፋውንዴሽኑ ቦርድ አባላት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ቀናት ተስብስበው እዚህ ውሳኔ ላይ መድረሳቸውም ታውቋል፡፡

የሽልማት ኮሚቴውን ውሳኔ አስመልክቶ አስተያየታቸውን የሰጡት ዶ/ር ሳሊም፣ ‹‹ሽልማቱ እ.ኤ.አ. በ2006 በይፋ ሲከፈት ደረጃው ከፍ ያለ እንዲሆን የተደረገው ታስቦበት ነው፡፡ በርካታ የአፍሪካ አገሮች መሪዎች አገሮቻቸውን ለመቀየር ላደረጉት ጥረት ዕውቅና እንሰጣለን፡፡ ነገር ግን የሽልማቱ ዓላማ ያልተለመዱ ልዩ የአመራር ክህሎቶችን ማጉላት ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ጉዳዩን በጥሞናና በጥንቃቄ ከመረመርን በኋላ ሽልማቱን እ.ኤ.አ. በ2016 ላለመስጠት ወስነናል፤›› ብለዋል፡፡

ለሞ ኢብራሒም ፋውንዴሽን ሽልማት ዕጩ በመሆን የሚቀርቡት የቀድሞ የአፍሪካ መሪዎች ሲሆኑ፣ ሥልጣናቸውን ከመታጨታቸው በፊት ባሉት ሦስት ዓመታት የለቀቁ መሆን አለባቸው፡፡ የሥልጣን ዘመናቸውም በዴሞክራሲያዊ ምርጫ የተገኘ መሆን አለበት፡፡

እስካሁን ሽልማቱ ለአራት የአፍሪካ የቀድሞ መሪዎች ተሰጥቷል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2014 ለናሚቢያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሂፊኪፑንዬ ፓሃምባ፣ እ.ኤ.አ. በ2011 ለኬፕ ቨርዴ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ፔድሮ ፒሬዝ፣ እ.ኤ.አ. በ2008 ለቦትስዋና የቀድሞ ፕሬዚዳንት ፌስተስ ሞሃይና እ.ኤ.አ. በ2007 ለቀድሞው የሞዛምቢክ ፕሬዚዳንት ጆአኪም ቺሳኖ ሽልማቱ መበርከቱ ይታወሳል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2007 ለቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላም በፋውንዴሽኑ የክብር ሽልማት ተሰጥቷል፡፡

ሞ ኢብራሒም ፋውንዴሽን በሱዳናዊና እንግሊዛዊ ቢልየነር የንግድ ሰው ዶ/ር ሞሐመድ ሞ ኢብራሒም እ.ኤ.አ. በ2006 የተቋቋመ ሲሆን፣ ዋነኛ ዓላማውም በአፍሪካ አመራር ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ነው፡፡

የሞ ኢብራሒም የአመራር ሽልማት አሸናፊ በቅድሚያ አምስት ሚሊዮን ዶላር የሚያገኝ ሲሆን፣ ከዚያ በኋላ በሕይወት እስካለ ድረስ 200,000 ዶላር በየዓመቱ ያገኛል፡፡

ባለሀብቱ ዶ/ር መሐመድ ሞ ኢብራሒም ፋውንዴሽኑን ለማቋቋም ስኬታማውን የቴሌኮሙዩኒኬሽን ኩባንያቸውን ሴልቴልን በ3.4 ቢሊዮን ዶላር እ.ኤ.አ. በ2005 መሸጣቸው ይታወሳል፡፡ 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 1275

Trending Articles