- ወደ ሰበር የሚሄዱ ይግባኞች ሳይታዩ ‹‹አያስቀርቡም›› መባላቸው ተጠቁሟል
- ለመልካም አስተዳደር ብልሹነት ተጠያቂዎቹ ፍርድ ቤቶች ናቸው ተብሏል
በመልካም አስተዳደር ዕጦት ወይም ብልሹ አሠራር የተማረረው የኅብረተሰብ ክፍል የመጨረሻው አማራጭ ወደ ሆኑት የፍትሕ አካላት የሚሄድ ቢሆንም፣ በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ ወይም በፍትሕ አካላት ውስጥ የሚገኙ ትንንሽ አምባገነኖች መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ ብሶቱን የሚያባብስ ድርጊት እየፈጸሙ፣ ወደ መጨረሻው የአመፅ አማራጭ እየገፉት መሆኑ ተገለጸ፡፡
ይኼ የተገለጸው ከሚያዝያ 30 ቀን እስከ ግንቦት 6 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ ‹‹የሕግ የበላይነት ለዘላቂ ሰላምና ለሕዝቦች አንድነት›› በሚል መሪ ቃል ለሰባተኛ ጊዜ የተከበረውን የፍትሕ ሳምንት አስመልክቶ፣ የፍትሕ አካላት የሚባሉት የፌዴራል ፍርድ ቤቶች፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደርና የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ግንቦት 2 ቀን 2009 ዓ.ም. በፍሬንድሺፕ ኢንተርናሽናል ሆቴል በጋራ ባዘጋጁት የአንድ ቀን አገር አቀፍ የውይይት መድረክ ላይ ነው፡፡
የፍትሕ አካላቱ ላለፉት ስድስት ዓመታት በተለያዩ መሪ ቃሎች ‹‹የፍትሕ ሳምንት›› እያሉ ያከበሯቸውና እያከበሩት ያሉት የፍትሕ ሳምንት በዓል፣ እርስ በርሳቸው ሳይግባቡ መሆኑን የመድረኩ ተሳታፊዎች ጠቁመዋል፡፡
መርማሪ ፖሊስ ከዓቃቤ ሕግ፣ እንዲሁም ፍርድ ቤቶች ከማረሚያ ቤቶች ጋር እንደማይግባቡ የጠቆሙት ተሳታፊዎቹ፣ በእነሱ አለመግባባት ሳቢያ ኅብረተሰቡ እየተጉላሉ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
መዝገቦች በፍርድ ቤቶች ከሚገመተው በላይ መብዛታቸውን የገለጹት የውይይቱ ተሳታፊዎች፣ ይኼ የሚያሳየው የፍትሕ አካላቱ የመልካም አስተዳደር ብልሹነት ፈጻሚዎች ላይ ጠንከር ያለ ዕርምጃ ባለመውሰዳቸውና ኅብረተሰቡ አማራጭ ሲያጣ ወደ ፍርድ ቤቶች ማምራቱ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በመልካም አስተዳደር ዕጦት ወደ ፍርድ ቤት የሚያመራው የኅብረተሰብ ክፍል ፍርድ ቤትም ትክክለኛ ፍትሕ አያገኝም ብለዋል፡፡ በሁለቱም ወገኖች ማለትም ብልሹ አሠራር እንዲሰፍን የሚያደርጉት አካላትና በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ በፖሊስ፣ በዓቃቤ ሕግ፣ በፍርድ ቤትና በማረሚያ ቤት ያሉ ወይም የተሾሙ ትንንሽ አምባገነን አመራሮች ኅብረተሰቡ አማራጭ እንዲያጣ እያደረጉት በመሆኑ በፍጥነት መስተካከል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ማኅበረሰቡ ፍትሕ ማግኘት ካልቻለ መጨረሻ ወደ ሆነው የአመፅ አማራጭ ውስጥ ስለሚገባ፣ ያ ከመሆኑ በፊት ግን የሚወሰደው ዕርምጃ ተወስዶ የሕግ የበላይነት መከበር እንዳለበት አስረድተዋል፡፡
የፍትሕ ሥርዓቱን ማስተካከልና ለሕግ የበላይነት መከበር ዕርምጃ መውሰድ ያለበት ከሕግ አወጣጥ ሥርዓት ጀምሮ መሆን እንዳለበት የጠቆሙት ተሳታፊዎቹ፣ ሕጎች ወዲያው ወዲያው እየወጡና እየተሻሩ ሕግ ተርጓሚውን ከሚያሳስቱት በደንብ ተመክሮባቸውና ውይይት ተደርጎባቸው በስለው መውጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
የፍትሕ ሳምንትን የሚያከብሩና እንዲከበር በጋራ እየሠሩ ያሉት አምስቱ የፍትሕ አካላት እየተገናኙና እየሠሩ ያሉት ተጠያቂነት በሌለበት ሁኔታ መሆኑን የገለጹት የውይይቱ ተካፋዮች፣ የሚመሩበት ወይም ግዴታ የሚወስዱበት አስገዳጅ ነገር በሌለበት በስምምነት ብቻ መሥራት ተጠያቂነት በሚመጣበት ጊዜ ‹‹የእኔ መደበኛ ሥራ ሌላ ነው…›› የሚል ሽሽት ወይም ከተጠያቂነት ውጪ መሆን እንደሚያመጣ ተናግረዋል፡፡ ተጠያቂነትን የሚያስከትል መመርያ መዘጋጀት እንዳለበትም አክለዋል፡፡ የፍትሕ ሳምንት ላለፉት ስድስት ዓመታት የተከበረ ቢሆንም ‹‹በዓል›› ከመሆን ያለፈ ፋይዳ እንዳልታየበትም ገልጸዋል፡፡ እያንዳንዱ ተቋም ምን እንደሠራና በዓመቱ ውስጥ ስላጋጠሙት ተግዳሮቶችና የተለያዩ ተሞክሮዎች መረጃ ለበላይ አካላት ሪፖርት ቢደረግም፣ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ አለመሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ጠበቆች ለፍትሕ አሰጣጥ ከፍተኛ ዕገዛ ስለሚያደርጉ የፍትሕ አካላቱ አብረዋቸው ቢሠሩ የተሻለ ውጤት ሊያስመዘግቡ እንደሚችሉ ተሳታፊዎቹ ጠቁመው፣ ጥራት ያለው የሕግ ባለሙያ ከማፍራት አንፃርም ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር እንዲሠሩ አሳስበዋል፡፡ ሕግ ቋንቋው ስለተጻፈ ብቻ ሳይሆን እንዴት እንደሚተገበር አውቆ ለመሥራት የማያቋርጥ ሥራ ማከናወንና ጥራት ያለው የሰው ኃይል ማፍራት ተገቢ መሆኑንም አክለዋል፡፡
የተሻለ ፍትሕ ለማግኘት ወይም ለመስጠት ለወንበሩ የሚመጥን፣ ብቃትና ጥራት ያለው የሰው ኃይል ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን የውይይቱ ተካፋዮች ገልጸው፣ በአሁኑ ጊዜ የፍትሕ ሥርዓቱ ትልቁ ተግዳሮት የብቃት ማነስና ሙስና መሆኑን አስምረውበታል፡፡
ፍትሕ በገንዘብ የሚመራ ከሆነ አገር እንደ አገር መቀጠል እንደማይቻል የተናገሩት ተወያዮቹ፣ ኅብረተሰቡን እያስጮኸው የሚገኘው ገንዘብ ያለው ውሳኔ እያስቀየረ የማይገባው መብት ማስከበር ሲችል፣ ደሃው የኅብረተሰብ ክፍል ግን ንፁህ መብቱን እያጣ መሆኑ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች አሁን ብልሹ አሠራር፣ ኪራይ ሰብሳቢነትና ሙስና ጣራ ላይ መድረሱን የሚያሳይ ‹‹ሙስና ሠፈር›› የሚል ስያሜ መሰጠቱን መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡ በዚህ ሥርዓት የተወለዱ ልጆች አመለካከታቸው ጥሩ እንዳልሆነ ጠቁመው፣ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ‹‹በእኛ ይብቃ› ብሎ ተባብሮ በትውልዱ ላይ መሥራት እንዳለበትም አስረድተዋል፡፡ ለጭቁን ሕዝቦች ነፃነት መስዋዕት የሆኑ ሰማዕታት ሰላምን ያረጋገጡ ቢሆንም፣ የፍትሕ አካላት ግን የሰማዕታቱን ውጤት ለማስጠበቅ እየሠሩ ባለመሆናቸው ኅብረተሰቡ ምሬቱ መብዛቱንም ደጋግመው አንስተዋል፡፡ ፍርድ ቤት ውስጥ ትንንሽ አምባገነኖች በመኖራቸው፣ ለውጥ ያመጣል ተብሎ የነበረው ቢፒአር እንኳን የውኃ ሽታ ሆኖ እንዲቀር ማድረጋቸውን አክለዋል፡፡
ፍርድ ቤቶች ውስጥ የአቅም ችግር እንዳለ የጠቆሙት የውይይቱ ተካፋዮች፣ በሥር ፍርድ ቤቶች የሚሰጡ ውሳኔዎች በብዛት ይግባኝ የሚሄዱትም ከአቅም ጋር በተያያዘ በሚሰጡ ውሳኔዎች ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በርካታ የሥር ፍርድ ቤቶች ውሳኔዎች ወደ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የሚሄዱ ቢሆንምና ‹‹ያስቀርባል ወይም አያስቀርብም›› ለማለት መዝገቦቹ መመርመር ቢገባቸውም፣ ሳይታዩ የተዘጉ መዝገቦች ብዙ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸውና የሕገ ሥርዓቱ አካል ያደረገቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ቢኖሩም፣ የሕግ ትርጓሜ በሚያስፈልግበት ወቅት ከድንጋጌው አንፃር መተርጎም የሚገባ ቢሆንም ተግባራዊ እየተደረጉ አለመሆኑንም አውስተዋል፡፡
የፍትሕ ሳምንት ሲከበር ለይስሙላ ወይም ለይምሰል መሆን እንደሌለበት የተናገሩት የውይይቱ ተካፋዮች፣ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥና የመልካም አስተዳደር ዕጦትም እንዲስተካከል ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ማሳተፍ ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ማረሚያ ቤቶች የታራሚን ሰብዓዊ መብት በማክበር ታርሞና ተጠብቆ እንዲወጣ ማድረግ ሲገባቸው፣ ፍርደኛው ከተፈረደበት ዓመታት በላይ አስረው እንደሚያቆዩ ተገልጿል፡፡ ክሱን በመከታተል ላይ የሚገኝን እስረኛ በቀጠሮው ቀን ወደ ፍርድ ቤት ማቅረብ ሲገባቸው፣ በመኪናና በአጃቢ አለመኖርና ሌሎች ምክንያቶች እንደማያቀርቡ በመጠቆም፣ ‹‹የፍትሕ አካላት ትብብር ታዲያ ምኑ ላይ ነው?›› በማለት ጠይቀዋል፡፡
የፍትሕ አካላት አቅም መፍጠር እንደሚገባቸው የተናገሩት ተሳታፊዎቹ አቅም የሌለው ፖሊስ፣ ዓቃቤ ሕግና ዳኛ ካለ ችግሮች መቼም ሊቀረፉ እንደማይችሉ አስረድተዋል፡፡ የፍትሕ አካላት ስለሕግ የበላይነት ግንዛቤ አለመኖር ለሰላም መደፍረስ ዋና ምክንያት እንደሚሆንም ተናግረዋል፡፡
ዳኛ በመሾምና የዲሲፕሊን ቅጣት በመጣል ብቻ ፍትሕ እንደማይገኝም አክለዋል፡፡ ለወንጀል መብዛት ዋናው ምክንያት ከክልሎች ወደ ፌዴራል ከተሞች የሚፈልሰው የሰው ብዛት መሆኑን የጠቆሙት ተሳታፊዎቹ፣ በዓመት ከ500 ሺሕ በላይ ሰዎች ወደ ከተሞች እንደሚገቡ ጠቁመዋል፡፡ ወንጀሉ በዋናነት ሌብነት መሆኑን፣ የተለያዩ ወንጀሎችም እንደሚፈጸሙና በፖሊስ፣ በዓቃቤ ሕግና በዳኛ የሚስተካከል አለመሆኑንም አስረድተዋል፡፡
የፍርድ ቤቶች ውሳኔ እንደማይፈጸምና በተለይ ከይዞታ ጋር በተገናኘ የሚሰጡ ውሳኔዎች የየክፍላተ ከተሞቹ ሥራ ከመሆኑ አንፃር፣ የመልካም አስተዳደር ዕጦት የት እንደደረሰ፣ ማን የማንን ትዕዛዝ እንደሚያስፈጽም የሥልጣን ተዋረዱ የጠፋበት አሠራር መስፈኑን አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ከኅብረተሰቡ ጋር በመተባበር የሕግ የበላይነትን ማስከበር እንዳለበት፣ የፍትሕ አካላትም ቅድሚያ ሰጥተው መሥራት ያለባቸው በዚህ ላይ መሆኑን የውይይቱ ተካፋዮች አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
የፍትሕ ሳምንቱን በማስመልከት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ በላቸው አንችሶ ‹‹ሰላምና ደኅንነት ለሕግ የበላይነት፣ ለዘላቂ ልማትና ለሕዝቦች አንድነት›› በሚል ርዕሰ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡ የውይይት መድረኩን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ዳኜ መላኩ፣ የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ደሳለኝ ረጋሳ፣ የፌዴራል ፖሊስ ተወካይና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ይህደጎ ሥዩም መርተውታል፡፡
