በዳዊት እንደሻው
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከተበዳሪዎች የወረሳቸውንና ወደፊትም የሚወርሳቸውን ድርጅቶች ማስተዳደር የሚያስቸለውን ኩባንያ ለማቋቋም መንግሥትን ጠየቀ፡፡
ባንኩ ኩባንያውን ለማቋቋም ከንግድ ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ኃላፊዎች ጋር መነጋገሩን፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታሁን ናና ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
አቶ ጌታሁን የሚቋቋመው ኩባንያ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ኮሜርሽያል ኖሚኒስ ዓይነት አወቃቀር እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡
ኮሜርሽያል ኖሚኒስ ቀድሞ ሞርጌጅ ባንክ ተብሎ በሚታወቀው በኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክና በንግድ ባንክ አማካይነት የተቋቋመ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ ይህ ድርጅት በንብረት አስተዳደር፣ በግብር ክፍያና ለሦስተኛ ወገን የሚደረጉ ክፍያዎች አገልግሎት ይታወቃል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የንብረት አስተዳደርና የካሳ ክፍያ አገልገሎቶች ይሰጣል፡፡
ከልማት ባንክ ጋር በተያያዘም የሚቋቋመው ኩባንያ በሥሩ የሚገኙ ተቋማትን ንብረት በዋናነት ያስተዳድራል፡፡
ኩባንያው ባንኩ ለሚያበድራቸው ብድሮች በመያዣነት ለሚይዛቸው ድርጅቶችና ብድሮቹ ሳይከፈሉ ሲቀሩ በባንኩ የሚወረሱ ድርጅቶችን ይከታተላል፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው ምንጮች እንደገለጹት፣ አሁን ባንኩ የሚወርሳቸውን ድርጅቶች ባለው የሕግ ውስንነት የተነሳ ማስተዳደር አስቸጋሪ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ባንኩ ይኼን አማራጭ ለመከተል እንደወሰነ አስረድተዋል፡፡
ከቀድሞው የልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ባህረ ኃላፊነታቸውን ከስድስት ወራት በፊት የተረከቡት አቶ ጌታሁን ከመጡ በኋላ፣ የተለያዩ ለውጦች እንዳደረጉ ይታወሳል፡፡ አቶ ጌታሁን ልማት ባንክ ከመምጣታቸው በፊት የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ እንደነበሩ ይታወሳል፡፡
በቅርቡም ባንኩን በምክትል ፕሬዚዳንትነት ሲመሩ የነበሩ አራት ኃላፊዎችን ከቦታቸው አንስተዋል፡፡
በምትካቸውም አቶ ጌታቸው ዋቄን የፕሮጀክት ፋይናንስ፣ አቶ ኃይለየሱስ በቀለን የብድር አስተዳደር፣ አቶ ሀዱሽ ገብረ እግዚአብሔርን የኮርፖሬት አገልግሎት፣ እንዲሁም አቶ እንዳልካቸው ምሕረቱን የባንኩ ፋይናንስና አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት አድርገው ሾመዋል፡፡
ኩባንያው የራሱን የመመሥረቻ ካፒታል ይዞ እንደሚቋቋምና ከንግድ ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጋር ሲደረግ የነበረው ምክክር መጠናቀቁን አቶ ጌታሁን ተናግረዋል፡፡
‹‹ፈቀዱን እንዳገኘን ኩባንያውን እናቋቁማለን፤›› ሲሉ አቶ ጌታሁን አክለዋል፡፡ ብሔራዊ ባንክ ባወጣው የዘጠኝ ወራት ሪፖርት መሠረት የልማት ባንክ የተበላሸ ብድር 16.1 በመቶ የደረሰ ሲሆን፣ እስካሁን ባንኩ ወደ 36 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ብድር ሰጥቷል፡፡
ባንኩ በዚህ ዓመት ብቻ እንደ ኤልሲ አዲስን የመሳሰሉ በከፍተኛ ገንዘብ የሚገመቱ ድርጀቶችን፣ እንዲሁም የተለያዩ የአበባ አምራች ድርጅቶችን ለሐራጅ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡
