Quantcast
Channel: ተሟገት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1275

የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣንን ንብረት በመዝረፍ የተከሰሱ ለብይን ተቀጠሩ

$
0
0
  • የንብረቱ ግምት ከ8.2 ሚሊዮን ብር በላይ ነው ተብሏል

የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ውስጥ በሚገኘው ፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ ግምጃ ቤት ያስቀመጣቸውን ንብረቶች በመዝረፍ፣ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል ተብለው ክስ የተመሠረተባቸው አሥር ግለሰቦች ለብይን ተቀጠሩ፡፡

ባለሥልጣኑ ከአጋር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ጋር ባለው ውል መሠረት ሁለት የጥበቃ ሠራተኞች የቀጠረ ቢሆንም፣ የጥበቃ ሠራተኞቹ አቶ ተሾመ አበበና አቶ ጎርፉ ጠንክር ከሌሎች ስምንት ተከሳሾች ጋር በጥቅም በመመሳጠር ግምታቸው 8,222,419 ብር የሆኑ 120 ዓይነት የቧንቧ ዕቃዎች እንዲዘረፉ ማድረጋቸውን፣ የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ የመሠረተባቸው ክስ ያስረዳል፡፡

በቅጽል ስሙ ‹አጃኤ› የሚባለው አቶ ተሻለ ገላን ከጥበቃ ሠራተኞቹ ጋር ከተመሳጠረ በኋላ፣ በቅጽል ስሙ ‹ሀብታሙ› የሚባለው አቶ ቡርቃ ሙለታ ለወንጀል ድርጊቱ ማስፈጸሚያ ካዋጣው 10,000 ብር ላይ 6,000 ብር ለጥበቃዎቹ በመስጠት፣ ዕቃዎቹን አቶ ጥላሁን ታደሰ በተባለው ተከሳሽ መጋዘን ውስጥ ማስቀመጣቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሮ አቅርቧል፡፡

በዝርፊያው ውስጥ በሾፌርነት፣ ዕቃውን በቤቱ ውስጥ በማስቀመጥ፣ የመጋዘኑን ቁልፍ ተመሳሳይ በመቅረጽ ከላይ የተጠቀሱትን ጨምሮ አቶ ማንደፍሮ ጌታቸው፣ አቶ አብዮት ከድር፣ አቶ ሲሳይ ሳህሌ፣ አቶ መኮንን ተመስገንና አቶ መስፍን ይትባረክ የተባሉ ግለሰቦች መሳተፋቸውን ዓቃቤ ሕግ ዘርዝሮ ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል፡፡

በግል ሥራ እንደሚተዳደር የተገለጸው ተከሳሽ አቶ መስፍን ይትባረክ ንብረቶቹ ከአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ተቋም የተዘረፉ መሆናቸውን እያወቀ፣ ከተቋሙ የተዘረፉትን ንብረቶች አቶ ሲሳይ ሳህሌ የተባለው ተከሳሽ በአይሱዙ ጭኖ የተወሰነ ርቀት ድረስ እንዲያደርስ ማድረጉን ክሱ ያብራራል፡፡ የተወሰነ ርቀት የወሰደውን ሾፌር በማስወረድና እንዳመመው በማስመሰል ሌላ ሾፌር ጠርቶ የተጫነውን ንብረት ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በሚገኘው አቶ ጥላሁን በተባለው ተከሳሽ መጋዘን ውስጥ እንዲራገፍ ማድረጉን ገልጿል፡፡ በተጨማሪም ለገበያ እንዲቀርብ ማድረጉን ዓቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ ፖሊስ ባደረገው ክትትል ግምታቸው 1,457,120 ብር የሆኑ ንብረቶች የተያዙ ቢሆንም፣ በድምሩ 8,222,419 ብር መንግሥት እንዲያጣ ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡

የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ክሱን የመሠረተው ከሦስት ዓመታት በፊት በ2006 ዓ.ም. ቢሆንም፣ በተለያዩ ምክንያቶች ክርክሩ እስካሁን ሊቆይ እንደቻለም ታውቋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ከቆጠራቸው ምስክሮች አብዛኞቹን አሰምቶ ሦስት ምስክሮች ለግንቦት 8 ቀን 2009 ዓ.ም. የተቀጠሩ ቢሆንም፣ አንዱ ብቻ ቀርቦ የምስክርነት ቃሉን ሲሰጥ ሁለቱ ሳይቀርቡ ቀርተዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ሁለቱን ምስክሮች ለማሰማት ቀጠሮ እንዲሰጠው የጠየቀ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡ በመሆኑም የቀረቡትን ምስክሮች ቃል ከተገቢው ሕግ በማገናዘብና በመመርመር ብይን ለመስጠት ለሰኔ 15 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 1275

Trending Articles